ስላሴ ወይም በእንግሊዝኛው Trinity የሚለው ቃል ሶስነትን የሚያሳይ ቃል ነው። የስላሴ ቃል ወይም ትምህርቱ በቀጥታ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ የለም፤ ሆኖም በብዙ የክርስትና ሃይማኖቶች ከዋናዎቹ አተምህሮቶች (doctrines) እንደ አንዱ የሚታይ ነው።
ይህ ትምህርት በመጀመሪያው የኒሲያ ጉባዬ ላይ ከክርስቶስ ልደት በኋላ በ325 ዓመተ ምህረት (እ.ኤ.አ) እንደ መሠረታዊ አተምህሮት የተወሰደ ትምህርት ነው።
የትምህርቱ መነሻ የሆነው በተለይ በአዲስ ኪዳን እግዚአብሔር፣ ኢየሱስ ክርስቶስና መንፈስ ቅዱስ አብረው የተጠቀሱባቸውን ክፍሎች ከሌሎች እግዚአብሔር አንድ ብቻ እንደሆነ ከሚናገሩ ክፍሎች ጋር እንዴት ማሳታረቅ ይቻላል ለሚለው ጥያቄ መልስ ለመስጠት ነው።
መጽሐፍ ቅዱስ ከብሉይ ኪዳን ጀምሮ እግዚአብሔር አንድ ብቻ እንደሆነ ይናገራል። ለምሳሌ፦
Quote:
ኦሪት ዘዳግም 6፡4 "እስራኤል ሆይ፥ ስማ አምላካችን እግዚአብሔር አንድ እግዚአብሔር ነው "
የማርቆስ ወንጌል 12፥29 "ኢየሱስም መልሶ እንዲህ አለው፦ ከትእዛዛቱ ሁሉ ፊተኛይቱ፤ እስራኤል ሆይ፥ ስማ፤ ጌታ አምላካችን አንድ ጌታ ነው"፥
በሌላ በኩል ደግሞ እግዚአብሔር፣ ኢየሱስ ክርስቶስና መንፈስ ቅዱስ አብረው የተጠቀሱባቸው ቦታዎች በአዲስ ኪዳን ይገኛሉ። ለምሳሌ፦
Quote:
2ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 13፡14 "የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የእግዚአብሔርም ፍቅር የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን። አሜን።"
የማቴዎስ ወንጌል 28፡19-20 "እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀ መዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ። "
የስላሴ ትምህርት እንግዲህ እንደዚህ ያሉትን ሁለት አይነት የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎች ለማስማማትና ለማስታረቅ የሚሞክር ትምህርት ነው። የትምህርቱም ይዘት የሚከተለውን ይመስላል፦
እግዚአብሔር አንድ ነው ሆኖም ሶስት ስብእናዎች (persons) አሉት። ስለዚህ አንድ እግዚአብሔር የሚባለው አብን፣ ወልድንና መንፈስ ቅዱስን አጠቃልሎ ነው የሚል ትምህርት ነው። ሶስቱም ራሳቸውን የቻሉና የማይበላለጡ እኩል ስብእናዎች (persons) ናቸው። ማለትም አብ ወልድ አይደለም ወይም ወልድ መንፈስ ቅዱስ አይደለም ወዘተ። እንዲሁም አብ ከወልድ አይበልጥም ወልድም ከመንፈስ ቅዱስ እኩል ነው ወዘተ። እናም አንድ እግዚአብሔር ሲባል ሶስቱን አጠቃልሎ ነው ብሎ የሚያምን ትምህርት ነው። ለዚህም ነው ይህን የሚያምኑ ክርስቲያኖች ብዙ ጊዜ እግዚአብሔር አብ፣ እግዚአብሔር ወልድ እና እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ እያሉ የሚጠሩት። ምንም እንኳን እንዲህ ያለ አባባል መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ባይገኝም።
የስላሴ ትምህርት ከዚህ በተጨማሪ የክርስቶስን መለኮታዊነት (divinity) ለማይቀበሉም መከላከያ የታሰበ ትምህርት ነው። ኢየሱስ ሰው ብቻ ነው ወይም ፍጥረት ብቻ ነው እንጂ አማላካዊ ባሕርይ የለውም የሚሉትንም ለመቃወም ኢየሱስን ከእግዚአብሔር እኩል አስተካክሎ በማስቀመጥ መልስ የሰጠ ትምህርት ነው።
የግሌ አስተያየት
በነገራችን ላይ የስላሴ ትምህርት ከክርስቶስ ልደት በኋላ ከ325 ዓመት በኋላ የመጣ ትምህርት መሆኑን ስለማያውቁ፤ ብዙ ክርስቲያኖች ይህ ትምህርት የደህንነት ዋናው ትምህርት ይመስላቸዋል። እናም በትምህርቱ ላይ ጥያቄ ያለው ሰው ልክ በክርስቶስ እንደማያምንና ከክርስቶስ ደህንነት እንደወደቀ አድርገው ነው የሚያዩት። ይሄ በእኔ አመለካከት ትክክል አይደለም። የትም ቦታ በመጽሐፍ ቅዱስ፤ አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ አንድ ላይ አንድ እግዚአብሔር ናቸው ብለህ ካላመንክ አትድንም የሚለ ነገር የለም። ስለዚህ መጽሐፍ ቅዱስን መሠረት ባደረገ እንዲሁም በትህትና ለመማር በሚፈልግ ልብ ሊጠየቅና ሊመረመር ይችላል ባይ ነኝ።
የስላሴ ትምህርት በአንድ ጎኑ፤ አንድ የታወቀ የመጽሐፍ ቅዱስ ታሪክ ሊቅ "የስላሴ ትምህርት ባይኖር ኖሮ ትምህርቱ መፈጠሩ አይቀርም ነበር" ብሎ እንዳለው፤ በእርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያሉ አንዳንድ ፍንጮች ወደ ስላሴ ትምህርት የሚያመለክቱ ይመስላሉ።
ሆኖም እንደ እኔ አመለካከት፤ ልክ የመጽሐፍ ቅዱስን አንድ ጫፍ ብቻ ይዘው "ኢየሱስ የተፈጠረ ሰው ብቻ ነው፤ ምንም መለኮታዊ ባሕርይ የለውም " እንደሚሉትና ወደ አንድ ጎን እንደሚለጥጡት፤ የስላሴ ትምህርት ደግሞ በተቃራኒው የተለጠጠ ነው ብዬ አምናለሁ።
ይሄን ያልኩበት መጽሐፍ ቅዱሳዊ የሆኑ ምክንያቶች አሉኝ።
- መጽሐፍ ቅዱስ ኢየሱስ መለኮታዊ ወይም አማላካዊ ባሕርይ እንዳለው በግልጽ ያስተምራል። እናም ኢየሱስ ልክ እንደ እግዚአብሔር አምልኮና ውዳሴ እንደሚቀበል ተጽፎአል። ሆኖም የኢየሱስን አማላካዊ ባሕርይ የጻፉት እነ ጳውሎስ ራሳቸው ግን አንድ እግዚአብሔር ሲሉ የትም ቦታ አብን፣ ወልድንና መንፈስ ቅዱስን በአንድ ላይ አድርገው አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ አንድ እግዚአብሔር ብሎ የሚጠራው ሁል ጊዜም ቢሆን አብን ብቻ ነው።
Quote:
„1ኛ ጢሞቴዎስ 2፣5 "አንድ እግዚአብሔር አለና፥ በእግዚአብሔርና በሰውም መካከል ያለው መካከለኛው ደግሞ አንድ አለ፥ እርሱም ሰው የሆነ ክርስቶስ ኢየሱስ ነው“
1ኛ ቆሮንቶስ 8፣5-6 „መቼም ብዙ አማልክትና ብዙ ጌቶች አሉ፤ ነገር ግን በሰማይ ሆነ በምድርም ሆነ አማልክት የተባሉ ምንም ቢኖሩ፥ ለእኛስ ነገር ሁሉ ከእርሱ የሆነ እኛም ለእርሱ የሆንን አንድ አምላክ አብ አለን፥ ነገር ሁሉም በእርሱ በኩል የሆነ እኛም በእርሱ በኩል የሆንን አንድ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስ አለን።“
ኤፌሶን 4፣4-6 „በመጠራታችሁ በአንድ ተስፋ እንደ ተጠራችሁ አንድ አካልና አንድ መንፈስ አለ፤ አንድ ጌታ አንድ ሃይማኖት አንዲት ጥምቀት፤ ከሁሉ በላይ የሚሆን በሁሉም የሚሠራ በሁሉም የሚኖር አንድ አምላክ የሁሉም አባት አለ።“
የማርቆስ ወንጌል 10፣18 „ኢየሱስም፦ ስለ ምን ቸር ትለኛለህ? ከአንዱ ከእግዚአብሔር በቀር ቸር ማንም የለም።“
1ኛ ጢሞቴዎስ 1፣17 „ብቻውን አምላክ ለሚሆን ለማይጠፋው ለማይታየውም ለዘመናት ንጉሥ ምስጋናና ክብር እስከ ዘላለም ድረስ ይሁን፤ አሜን።“
1ኛ ጢሞቴዎስ 6፣16 „እርሱ ብቻ የማይሞት ነው፤ ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን ይኖራል፤ አንድ ሰው እንኳ አላየውም ሊያይም አይቻለውም፤ ለእርሱ ክብርና የዘላለም ኃይል ይሁን፤ አሜን።“
ስለዚህ አንድ እግዚአብሔር ማለት ሶስቱን ማለትም አብን፣ ወልድንና ኢየሱስን በአንድነት አጠቃልሎ ነው የሚለው የስላሴ ትምህርት ፈጽሞ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የለም። መጽሐፍ ቅዱስ ሁሌም አንዱ እግዚአብሔር እያለ የሚጠራው አብን ብቻ ነውና።
እነ ጳውሎስ ታዲያ በአንድ በኩል ኢየሱስ መለኮታዊና አምላካዊ ባሕርይ እንዳለው ይጽፋሉ፤ ይህም ሆኖ ግን አንዱ እግዚአብሔር የሚባለው ግን አብ ብቻ እንደሆነም ይናገራሉ። ኢየሱስ መለኮታዊ ባሕርይ ስላለው፤ ያ ከብሉይ ኪዳን ዘመን ጀምሮ አንዱ እግዚአብሔር እየተባለ ሲጠራ የነበረው አብ ውስጥ ኢየሱስንና መንፈስ ቅዱስን ደምረው በአንድነት ነው አንዱ እግዚአብሔር የሚባለው ወደሚል መደምደሚያ አልደረሱም። ኢየሱስ መለኮታዊና አምላካዊ ባሕርይ አለው? አዎ ሆኖም ግን አሁንም ቢሆን አንዱ እግዚአብሔር ብለው እነ ጳውሎስ የሚጠሩት አብን ብቻ ነው። ይህ ከስላሴ ትምህርት ይለያል።
- አብም፣ ኢየሱስም፣ መንፈስ ቅዱስም የማይበላለጡ እኩል ናቸው የሚለው የስላሴ ትምህርት በእኔ አመለካከት መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት የለውም። መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽና በማያወላውል ሁኔታ ኢየሱስ ከአብ እንደሚያንስና አብ ኢየሱስን መብለጥ ብቻ ሳይሆን የኢየሱስ አምላክም እንደሆነ ተጽፎአል።
ይህ ደግሞ ብዙዎች እንደሚመስላቸው ኢየሱስ በምድር እንደ ሰው ሲመላለስ ብቻ አይደለም። ኢየሱስ "ከእኔ አብ ይበልጣል" ሲል ብዙ የስላሴ አማኞች የሚመስላቸው ኢየሱስ በአምላክነቱ ሳይሆን በሰውነቱ ራሱን ከእግዚአብሔር ጋር እያወዳደረ ይመስላቸዋል። ሰውማ ከእግዚአብሔር እንደሚያንስ እንኳን አይሁዳዊ የሆኑ ደቀመዛሙርቱ ይቅርና አሕዛብም ያውቃሉ። ኢየሱስ ወልድን ወይም አማላካዊ ባሕርይውን ነው ከአብ ጋር የሚያወዳድረው። ይህ ብቻ አይደለም ከሙታን ተነስቶ በአብ ዘንድ በክብርም ከሆነ በኋላ አሁንም ከአብ እንደሚያንስ የሚያሳዩ ነገሮች በራእይ መጽሐፍ ላይ ተጽፈዋል።
እስቲ አንዳንድ ምሳሌዎችን እንመልከት፦
Quote:
የዮሐንስ ወንጌል
5፥26 አብ በራሱ ሕይወት እንዳለው እንዲሁ ደግሞ ለወልድ በራሱ ሕይወት እንዲኖረው ሰጥቶታልና።
Amplified Bible
John 5:26 "For even as the Father has life in Himself and is self-existent, so He has given to the Son to have life in Himself and be self-existent."
በዚህ ክፍል የምንመለከተ ወልድ የአብ አይነት self-existent ሕይወት እንዳለው የሚናገር ነው። ማለትም ሕይወት በራሱ ያለውና ሕይወትን ማመንጨት የሚችል ሕይወት አብ እንዳለው እንዲሁ ወልድ አለው። ይህን መቼም ኢየሱስ የሚናገረው ስለ ምድራዊ ሕይወቱ እንዳልሆነ ግልጽ ነው። ታዲያ ይህን የአብ አይነት self-existent የሆነ ሕይወት እንኳን ለኢየሱስ የሰጠው አብ እንደሆነ ነው የሚናገረው።
ይህም ብቻ አይደለም የሚከተለቱም ክፍሎች ሁሉ የሚያሳዩት አብ የኢየሱስ የበላይ ጌታና አምላክ እንደሆንና ኢየሱስ ደግሞ የአብ ታዛዥ ልጅና የበታች እንደሆነ ነው።
Quote:
1ኛ ቆሮንቶስ 11፡3 „ነገር ግን የወንድ ሁሉ ራስ ክርስቶስ፥ የሴትም ራስ ወንድ፥ የክርስቶስም ራስ እግዚአብሔር እንደ ሆነ ልታውቁ እወዳለሁ።“
ዮሐንስ 5፡19 „ስለዚህ ኢየሱስ መለሰ እንዲህም አላቸው፦ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ አብ ሲያደርግ ያየውን ነው እንጂ ወልድ ከራሱ ሊያደርግ ምንም አይችልም፤ ያ የሚያደርገውን ሁሉ ወልድ ደግሞ ይህን እንዲሁ ያደርጋልና።“
የዮሐንስ ወንጌል 14፥28 "እኔ እሄዳለሁ ወደ እናንተም እመጣለሁ እንዳልኋችሁ ሰማችሁ። የምትወዱኝስ ብትሆኑ ከእኔ አብ ይበልጣልና ወደ አብ በመሄዴ ደስ ባላችሁ ነበር።"
ኢየሱስ ራሱ ሲናገር ስለ ዓለም ፍጻሜ፤ ስለዚያች ቀንና ሰዓት ከአብ በስተቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ወልድም ቢሆን እንደማያውቅ ተናገሮአል። ይህም ብቻ አይደለም፤ በራእይ መጽሐፍ ለዮሐንስ የተገለጠለት ራእይ ራሱ፤ አብ ለኢየሱስ የሰጠው ራእይ እንደሆነ ተጽፎአል።
Quote:
የማቴዎስ ወንጌል 24፣36 „ስለዚያች ቀንና ስለዚያች ሰዓት ግን ከአባት ብቻ በቀር የሰማይ መላእክትም ቢሆኑ ልጅም ቢሆን የሚያውቅ የለም።“
የዮሐንስ ራእይ 1፡1 "ቶሎ ይሆን ዘንድ የሚገባውን ነገር ለባሪያዎቹ ያሳይ ዘንድ እግዚአብሔር ለኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠው በእርሱም የተገለጠው ይህ ነው፥ ኢየሱስም በመልአኩ ልኮ ለባሪያው ለዮሐንስ አመለከተ፥ "
ከትንሳኤም በኋላ እግዚአብሔር የኢየሱስ አምላክ እንደሆነና ከኢየሱስ የሚበልጥ እንደሆነ ብዙ የሚያሳዩ ጽሑፎች በአዲስ ኪዳን እናገኛለን። ሁለቱን ለመጥቀስ ያህል፦
Quote:
1ኛ ቆሮንቶስ 15፣27-28 „ሁሉን ከእግሩ በታች አስገዝቶአልና። ነገር ግን፦ ሁሉ ተገዝቶአል ሲል፥ ሁሉን ካስገዛለት በቀር መሆኑ ግልጥ ነው። ሁሉ ከተገዛለት በኋላ ግን እግዚአብሔር ሁሉ በሁሉ ይሆን ዘንድ በዚያን ጊዜ ልጁ ራሱ ደግሞ ሁሉን ላስገዛለት ይገዛል።“
የዮሐንስ ራእይ 3፣12 „ድል የነሣው በአምላኬ መቅደስ ዓምድ እንዲሆን አደርገዋለሁ፥ ወደ ፊትም ከዚያ ከቶ አይወጣም፤ የአምላኬን ስምና የአምላኬን ከተማ ስም፥ ማለት ከሰማይ ከአምላኬ ዘንድ የምትወርደውን አዲሲቱን ኢየሩሳሌምን፥ አዲሱንም ስሜን በእርሱ ላይ እጽፋለሁ።“
ማጠቃለያ
መጽሐፍ ቅዱስ በግልጽ ኢየሱስ መለኮታዊና አምላካዊ ባሕርይ ያለው የዛ የአንዱ እግዚአብሔር ልጅ እንደሆነ ያስተምራል። ኢየሱስ የዛ የአንዱ እግዚአብሔር የማይታየው ባሕርይ መገለጫና የክብሩ መንጸባረቂያም እንደሆነ ተጽፎአል። ሆኖም ግን ያ አንዱ እግዚአብሔር፤ አብን ወልድንና መንፈስ ቅዱስን በአንድነት አጠቃልሎ ነው የሚል ነገር አያስተምርም። ይባስ ብሎ ደግሞ አብና ኢየሱስ አይበላለጡም የሚባል ትምህርት ፈጽሞ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አይገኝም።
በአንድ በኩል ኢየሱስ አማላካዊ ባሕርይ እንደሌለውና ሰው ብቻ እንደሆነ የሚል ትምህርት በተቃራኒው በሌላ በኩል ደግሞ አንዱ እግዚአብሔር የሚባለው ሶስቱም በአንድነት ነው እናም ኢየሱስም ከአንዱ ከእግዚአብሔር ጋር እኩል ነው የሚል ትምህርት ሁለቱም የተለጠጡና ሚዛናዊውን የመጽሐፍ ቅዱስ ትምህርት የሚያንጸባርቁ አይደሉም እላለሁ።
እነ ጳውሎስ አንዱን እግዚአብሔርን አብን፤ ብቸኛ አምላክ እያሉም እንዲሁ ደግሞ የኢየሱስን አምላካዊ ባሕርይ ይቀበሉ ነበር። እኛም እንዲህ ልናደርግ ይገባል እላለሁ።
Quote:
ወደ ዕብራውያን 1፥3 "እርሱም የክብሩ መንጸባረቅና የባሕርዩ ምሳሌ ሆኖ፥ ሁሉን በስልጣኑ ቃል እየደገፈ፥ ኃጢአታችንን በራሱ ካነጻ በኋላ በሰማያት በግርማው ቀኝ ተቀመጠ፤"
ቆላስይስ 1፣15 „እርሱም የማይታይ አምላክ ምሳሌ ነው።“