Quote:
መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 1
6እግዚአብሔርም ማኅፀንዋን ዘግቶ ነበርና ጣውንትዋ ታስቆጣት ታበሳጫትም ነበር።
ሐና ልጅ ስለሌላት ፍናና ስታስቆጣትና ስታበሳጫት፡ ሐናም ስታዝንና ስታለቅስ በልብዋም ስትመረረ እግዚአብሔር ይህን ሁሉ ጉዳይ ሳያውቅ ቀርቶ አይደለም። እንዲያውም መጽሐፍ ቅዱስ ማኅፀንዋን የዘጋው ራሱ እግዚአብሔር እንደሆነ ነው የሚነግረን። ስለዚህ እንኳን በእኛ በልጆቹ ይቅርና በትንሹዋ ወፍ (ድንቢጥ) ላይ እንኳን የሚደረሰውን ነገር እግዚአብሔር ሳያውቅና ሳይፈቅድ አይሆንም።
Quote:
የማቴዎስ ወንጌል 10
29ሁለት ድንቢጦች በአምስት ሳንቲም ይሸጡ የለምን? ከእነርሱም አንዲቱ ያለ አባታችሁ ፈቃድ በምድር ላይ አትወድቅም። 30የእናንተስ የራሳችሁ ጠጉር ሁሉ እንኳ ተቈጥሮአል።
31እንግዲህ አትፍሩ ከብዙ ድንቢጦች እናንተ ትበልጣላችሁ።
ብዙ ጊዜ አይግባንም እንጂ እግዚአብሔር ጸሎትን ያልሰማ ቢመስለንም እንኳን በሕይወታችን ጌታ የሚያደረገው ነገር ለመልካም ነው።
እርሱን ሳይሆን የእግዚአብሔርን ስጦታና በረከት ብቻ በሚፈልጉት እግዚአብሔር ደስ አይሰኝም። ኢየሱስ ክርስቶስ አምስት እንጀራንና ሁለት ዓሣን አብዝቶ ለአምስት ሺህ ሰዎች ከመገበ በኋላ ምግብ እንደሚሰጥ አይተው ምግብን ፍለጋ የተከተሉትንም ሰዎች እንዲህ ነበር ያላቸው፦
Quote:
የዮሐንስ ወንጌል 6
26ኢየሱስም መልሶ፦ እውነት እውነት እላችኋለሁ፥ የምትፈልጉኝ እንጀራን ስለ በላችሁና ስለ ጠገባችሁ ነው እንጂ ምልክቶችን ስላያችሁ አይደለም።
ነፍሱን በመስቀሉ ላይ የሰጠንንና ከዘላለም ፍርድ ወደ ዘላለም ሕይወት የጠራንን የእግዚአብሔር ልጅን ኢየሱስን የምንከተለው ምግብ ስለምሰጠን፤ ከድህነት ስለሚያወጣን፤ ትዳር ወይም ልጅ ስለሚሰጠን አይደለም። እነዚህን ሁሉ ኢየሱስን የማይከተሉና የማያምኑ አህዛብም ሁሉ ያገኙታል። የእኛ ተስፋ ምድራዊ አይደለም። ተስፋችን አንድ ቀን በምድር ላይ ደልቶን የመኖር ወይም አንድ ቀን ኑሮና ትዳር ተሳክቶልን በዚህች ምድር የመኖር ተስፋ አይደለም። እንዲህም አይነት ተስፋ ጌታ አልሰጠንም። እንዲያውም በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ ነው ያለን። ስለዚህ የመከራውን መስቀል ተሸክማችሁ እንጂ ምድራዊ በረከቴን እየበላችሁ ተከተሉኝ አላለንም። በዚህች ምድራዊ ሕይወት ብቻ ኢየሱስን ተስፋ ያደረግን ከሆነ ደግሞ ምንኛ ምስኪን ነን ይላል መጽሐፍ ቅዱስ።
Quote:
1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች
15፥19 በዚች ሕይወት ብቻ ክርስቶስን ተስፋ ያደረግን ከሆነ፥ ከሰው ሁሉ ይልቅ ምስኪኖች ነን።
እኛ የተጣራነው በአንደኛ ደረጃ ሰማያዊና ዘላለማዊ ለሆነ ለማይጠፋ ተስፋ ነው። በዚህች አጭር የእድሜ ዘመናችን በምድር እንግዶችና ምጻተኞች እንጂ ተመቻችቶ ነዋሪዎች አይደለንም። በዚህ የምናፈራው ሃብትም ይሁን ትዳር ሁሉም አላፊና ጊዜያው ነው። ክርስቶስ የተሰቀለልን ግን ለዘላለማዊ ማደሪያችን ነው። የዚህች ምድር በረከቱዋ ብቻ ሳይሆን መከራዋና ለቅሶዋም እንዲሁ አላፉ ነው። ለዘላለም እንባችንን ከአይናችን የሚያብስልን ጌታ ጋር ስንሄድ እንባችን ለዘላለም ይታበሳል።
ስለዚህ በዚህች አጭሩዋ ምድራዊ ሕይወታችን በጊዜያዊውና አላፊው በምድር በረከትና ስጦታ ምክንያት ዘላለማዊውንና ክርስቶስ የሞተልንን ሰማያዊውን ተስፋና በረከት እንዳናጣው መጠንቀቅ ይኖርብናል። የእግዚአብሔር ምድራዊ ስጦታ ቀረ ብለን የዘላለሙን እንዳናጣው፡ ኤሳው እንዳደረገው የከበረውን በማይረባው እንዳንለውጠው እንጠንቀቅ።
ይልቁን እንደ ሲድራቅ፣ ሚሳቅና አብደናጎም አምላካችን ከሚነድደው ከእሳቱ እቶን ቢያድነንም ባያድነንም ላቆምከው ምስል አንሰግድም ብለው እንደቆረጡት፡ እኛም ይሄ ወይም ያ በረከት መጣ ወይም አልመጣ እኛ ግን የተሰቀለልንን የዘላለሙን ተስፋችንን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ከመከተል ወደ ኋላ አንልም የሚል የልብ አቋም ይኑረን።
ወንድማችን ሆይ፦ ዘመኑ እውነተኛው ክርስትና መስቀልን ተሸክሞ ጌታን መከተል የሚለውንና እንደ ምጻተኞች በዚህች ሃላፊ ምድር የመኖር ነገር የተረሳበትና ጌታን ምግብ ለመብላት ብቻ እንደተከተሉት ሰዎች ኢየሱስ የምግብና የመኪና የትዳርና የቤት ወዘተ ሰጪ ብቻ ተደርጎ ክርስትና በዚህች አጭር ሕይወታችን የምድራዊውን ሕይወታችንን ብቻ አሳክተን የምንኖርበት ዘዴ ተድርጎ ዋናው ወንጌል የተራሳበት ዘመን ነው። ስብከቱም ትንቢቱም ከመስቀሉ ቃል ወጥቶ ወደ ይሳካልሃልና ይባርክሃል የተገባበት፤ ከዘላለማዊው ወደ ጊዜያዊው፣ ከማይጠፋው ወደሚጠፋ ፈቀቅ የተባለበት ጊዜ ነው። አማኞች ከጌታ ጋር ያላቸው ግንኙነት ምድራዊ በረከት ከመቀበልና ካለመቀበል ያልዘለቀ እየሆነ ነው። በመስቀል ላይ ነፍሱን በመስጠት የተገለጠውና ከሁሉ የሚበልጠው የጌታችን ፍቅር እንኳን በጥርጣሬ የሚታይበትና የፍቅር መለኪያ ምድራዊና ጊዜያው በረከት እየሆነ የመስቀሉ ፍቅር እየተረሳ የመጣበት ዘመን ነው። ስለዚህ ምንም እንኳን እኔ የትዳርን ፍላጎት ግፊት ጠንቅቄ ባውቀውም ከሁሉም በላይ ሃላፊው ትዳር በአንተና በነፍስህ እረኛ መካከል እንዳይገባ እንድትጠነቀቅ አጥብቄ እመክርሃለሁ።
በሌላ በኩል ደግሞ ሰው በጌታ እንጂ በትዳር ደስተኛ እንደማይሆን አሁንም ከብዙዎች ልምድ እውነቱን ልነግርህ እወዳለሁ። ትዳር ትዳር ብለው ለምነውና አልቀሰው ከገቡት ውስጥ ብዙዎች በትዳር ደስተኞች አይደሉም። እንዲያውም ያንን የብቸኝነትና "የነጻነት" ጊዜ የሚናፍቁ ጥቂቶች አይደሉም።
ስለዚህም ይመስለኛል ሐዋርያው ጳውሎስ ሲመክር ከትዳር ውጪ ያሉትን ትዳር መታሰር እንደሆነና ብዙ ፈተናም እንዳለው ስለሚያውቅ ይሄን ያክል ትዳርን እንዳይመኙት የሚያሳስበው። እንዲያውም ወደ ትዳር የሚገቡ ሰዎች በዚህ አለም ብዙ ችግር እንደሚገጥማቸውና ጳውሎስም ይህ እንዳይሆንባቸው እንደሚፈልግ ይገልጻል። በትዳር ውስጥ ያሉት ደግሞ በሰበብ ባስባቡ ከትዳር የመውጣትና "ነጻ" ለመሆን የመፈለግ ፈተና እንዳለ ተረድቶ፡ መፋታታን እንዳይፈልጉ ይመክራል።
Quote:
1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች
27በሚስት ታስረህ እንደ ሆንህ መፋታትን አትሻ፤ በሚስት አልታሰርህ እንደ ሆንህ ሚስትን አትሻ።
28ብታገባ ግን ኃጢአት አትሠራም ድንግሊቱም ብታገባ ኃጢአት አትሠራም፤ ነገር ግን እንዲህ በሚያደርጉ በሥጋቸው ላይ መከራ ይሆንባቸዋል፥ እኔም እራራላችሁ ነበር።
1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች (አዲሱ መደበኛ ትርጉም)
28 ነገር ግን የሚያገቡ ሰዎች በዚህ ዓለም ብዙ ችግር ይገጥማቸዋል፤ እኔም ይህ እንዳይደርስባችሁ እወዳለሁ።
እግዚአብሔር አባታችን ነው። አባት ደግሞ ለልጆቹ መልካምን ነገር ነው የሚያስብላቸው። ልጁን የሚወድ አባት ሁሉ ልጁ የሚለምነውን ሁሉ አይሰጠውም። መማር ያለበትን ይስተምረዋል፤ መቀረጽ ያለበትን ይቀርጸዋል። ልጆቹ የለመኑትን አሁን ባይሰጣቸው ወይም ጭራሹን ቢከለክላቸው፡ ለእነርሱ አስቦ እንጂ ጠልቶአቸው ወይም ሊጎዳቸው ስለፈለገ አይደለም። ለእኛ አስቦ እንጂ እንኳን ምድራዊና ጠፊ ስጦታ ይቅርና አንድያ ልጁንም እንኳን ሰጥቶናል። የእግዚአብሔር ፍቅር ልክ እንደ ማንኛውም መልካም አባት ሁሉ በመስጠት ብቻ ሳይሆን በማዘግየትና በመከልከልም ይገለጻልና።